የሀገር ውስጥ ዜና

በጎፋ ዞን በአደጋው ከተፈናቀሉት በተጨማሪ ስጋት ያለባቸው ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ ይሻሉ ተባለ

By Shambel Mihret

July 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎፋ ዞን በአደጋው ተፈናቅለው እርዳታ ከሚሹት በተጨማሪ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ከ6 ሺህ በላይ ዜጎችድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር) እንዳሉት÷በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው አደጋ ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ተለይተዋል፡፡

በአደጋው ተፈናቅለው ለሚገኙ ከ200 በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ እርዳታ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ስጋት ባለበት አከባቢ ያሉና ድጋፍ የሚሹ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በአደጋው የተፈናቀሉትን ከስጋት ነጻ በሆነ አካባቢ በዘላቂነት ለማስፈር እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከፌዴራልና ከክልል በተወጣጡ ባለሙያዎች አካባቢው ላይ የአደጋ ሁኔታው ጥናት መደረጉን ጠቁመው÷ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአደጋው የተፈናቀሉትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ከመርዳት በተጨማሪ የስነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አመላክተዋል።

በታሪኩ ለገሰ