አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራር አባላት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ባለው የምላሽ ሥራ ላይ መከሩ ።
ምክክሩ የተካሄደው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ሥጋት ምክር ቤትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሆኑ ተመልክቷል።
በምክክር መድረኩ በአሁን ወቅት እየተደረገ ያለው አስቸኳይ የአደጋ ምላሽ ሥራ መገምገሙን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጎጂዎችን በቋሚነት ለማቋቋም ብሎም በጥናት ላይ ተመስርቶ ዳግም አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል በሚደረገው ተግባር ላይ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም (ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልልና የዞን አመራር አባላት ተሳትፈዋል።