የሀገር ውስጥ ዜና

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያና አረንጓዴ ሽግግር ለመደገፍ ቁርጠኝነቱን ገለጸ

By Meseret Awoke

July 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አረንጓዴ ሽግግር ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት የዘላቂ ፋይናንስ ዳይሬክተር አንቲ ካርሁነን ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በምታደርገው ጥረት ዙሪያ መክረዋል፡፡

ሚኒስትሯ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የሽግግር የፍትሕ ስርዓት የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት ሊጠናቀቅ መቃረቡን ገልጸው ፥ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነትና የኢንቨስትመንት መስህብነት በማጎልበት የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ ግጭቶች፣ የዩክሬን ጦርነት እና በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰቱ እንደ ድርቅ ያሉ የአየር ንብረት ነክ ጉዳዮች አንዳንድ የማሻሻያ ጥረቶች እንዲስተጓጎሉ እንዳረጉም አመላክተዋል፡፡

ካርሁነን በበኩላቸው እንዳሉት ፥ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያና አረንጓዴ ሽግግር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጌትዌይ እስትራቴጂ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።

በአውሮፓ ህብረት ሁለገብ ዓመታዊ አመላካች ፕሮግራም ስር ለኢትዮጵያ የተመደበውን 650 ሚሊየን ዩሮ አንዱ የድጋፉ አካል መሆኑን ነው ያነሱት።

ሚኒስትሯ ፥ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ወሳኝ የሆነው የአውሮፓ ህብረት የበጀት ድጋፍ እንደገና እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።

የተጣደፈ ትግበራ በሚሊየን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾችን ሊጎዳ እንደሚችል እና የአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ-ነጻ ደንብ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች ትክክለኛ የሽግግር መርሆዎች ጋር ሙሉ በሙሉ መጣጣም እንዳለበት አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የደንቡ መስፈርቶችን ለማሟላት ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀው ÷ ለትግበራው የሚረዳ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት፡፡

ዳይሬክተሩ በቅርቡ በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መደርመስ ባስከተለው አሰቃቂ አደጋ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ፌደራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እየሰራ በሚገኘው ቡድን በኩል ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም ነው የገለጹት።

ሚኒስትሯ ለአውሮፓ ህብረት ፈጣን ምላሽ አድናቆታቸውን ገልፀው ፥ ከአፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን ዘላቂ የአየር ንብረት መላመድ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡