አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 45 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የገንዘብ እና ቁሳቁስ ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ገዜ ጎፋ ወረዳ መላኩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በድጋፉ ሽኝት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለወገን ቀድሞ መድረስ ቀዳሚ ተግባራችን ነው ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬቾ ቀበሌ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን የመጀመሪያ ዙር 45 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ እና ቁሳቁስ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ቦታው ተልኳል።
ከተላኩት የድጋፍ አይነቶቹ ውስጥ አምቡላንስ፣ የህፃናት አልሚ ምግቦች ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና እርዳታ መስጫ መሣሪያዎች ፣ መድሃኒቶች፣ እንሶላዎችና ብርድ ልብሶች እንደሚገኙበት መጥቀሳቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
የከተማው አመራሮች ወደ ቦታው በአካል የሄዱ ሲሆን የጉዳቱን ልክ በቦታው በአካል በማየት ድጋፉን ለመቀጠል እንሰራለን ሲሉም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ዜጎች በደረሰባቸው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ህዝቡ ሁሌም ከጎናቸው መሆኑን አረገግጠዋል።