Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ስራዎች ስኬት ሚናችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን – የሀገር ሽማግሌዎች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለጀመራቸው ስራዎች ስኬት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የጋምቤላ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የሀገር ሽማግሌዎቹ እንደገለጹት÷ ኮሚሽኑ እያከናወነ ባለው የምክክርና ውይይት ሂደት እንደ ሀገር ሽማግሌነታቸው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ኡዶል አጉዋ÷ ምክክሩ በተለይም እንደ ሀገር የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል ደግሞ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተጀመሩ ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ተባብሮ መስራት አለበት ብለዋል።

እንደ ሀገር ሽማግሌነታቸው የኢትዮጵያውያንን የቆየ የአብሮነትና የአንድነት እሴትን ለአዲሱ ትውልድ በማስረዳት የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህልና ልምድን በመጠቀም ለሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንደሚሰሩም ነው አቶ ኡዶል የገለጹት።

ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በማስወገድ በአንድነት የመኖር እሴትን በማጠናከር ለሀገር እድገትና ልማት መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የጋምቤላ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ማቲዎስ መሰኒ ናቸው።

ሰላም በመንግስት ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችል ጠቁመው÷ ሁሉም ዜጋ መልካም ሀሳቦችን በማፍለቅና በማዋጣት ለሀገሩ ዘላቂ ሰላም ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈቱ ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚሰሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ አሳታፊ በሆነ መልኩ ልዩነቶች በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ ሌለው የጋምቤላ ከተማ አስተያየት ሰጪ ፓስተር ማን ሙን ናቸው።

በመሆኑም ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱና የቀድሞው መተሳሰብ፣ ፍቅርና አንድነት እንዲጸና እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version