Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሶማሌ ክልል ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚ መሆን ችሏል-አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ህዝብ ላለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚ መሆን መቻሉን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለፁ።

በሶማሌ ክልል መንግስት በተመደበ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው 2ኛ ዙር የጅግጅጋ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ተመርቋል።

በፕሮጀክቱ ከጉድጓድ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ማጠራቀሚያ 47 ኪሎ ሜትር እና አጠቃላይ 77 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታም ተከናውኗል።

የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ሻፊ አህመድ (ኢ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት የከተማውን የውሀ አቅርቦት ሽፋን 50 በመቶ በማሳደግ የውሀ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ያስችላል ብለዋል።

11 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ያሉት ይህ ፕሮጀክት፣ ከ500 እስከ 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሀ የመያዝ አቅም ያላቸው ሪዘርቫየሮች ያሉት ሲሆን÷ ለፕሮጀክቱ ግንባታ በግብዓትነት የዋሉ ሁሉም መሳሪያዎች ዘመናዊ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው÷ የክልሉ ህዝብ ላለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

ባለፉት ስድስት አመታት በክልሉ በርካታ ከተሞችና ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የተከናወነላቸው ሲሆን÷ ከእነዚህ መካከልም ጎዴይ፣ ዋርዴር ፣ አዋሬ ፣ ሺላቦ፣ ቱሊ ጉሌድ ፣ ሸበሌይ፣ መርማርሳ፣ ጅግጅጋ እና ሌሎችም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የንፁህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ሙስጠፌ የክልሉ ህዝብ በእድገት ጎዳና መራመድ ችሏል ያሉ ሲሆን÷ህዝቡ በለውጡ የተገኘውን ሰላምና ልማት በማጠናከር ማስቀጠል ይገባዋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version