አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያን ከመቃወም ይልቅ ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያን ቢደግፉ በብዙ ያተርፋሉ ሲል የቱርኩ የዜና ምንጭ ዴይሊ ሳባህ ገለጸ፡፡
የዜና ምንጩ ባስነበበው ጽሁፍ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ያልተነገረለት ነው ሲል ገልጿል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ሊቆይ ይችላል ይላሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሰው ልጆች ምክንያት የሚፈጠር እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን፥ ይህም የዓለምን ከባቢ አየር የሚቀይር እንደሆነ ነው የሚጠቁመው፡፡
ተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለውጥ መከሰቱ ለምድር እና በውስጧም ለያዘቻቸው ለሰው ልጆች ከባድ ፈተና ነው፥ በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጅን ህልውና የሚፈትን በመሆን የዓለም ስጋት መሆኑን ዘገባው አንስቷል፡፡
ከፈረንጆቹ 1980ዎቹ ጀምሮ ዓለም የከፋ የአየር ሁኔታ፣ ተደጋጋሚ እና ከባድ የሙቀት ማዕበል፣ በረሃማነት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአርክቲክ በረዶ መቅለጥ፣ የብዝሀ ህይወት መመናመን፣ የመሬት መራቆት፣ የምርታማነት መቀነስ እና ሌሎች በርካታ ፈተናዎች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠሟት ነው።
በዚህ ረገድ በተለይ ካደጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዝ አካባቢን በመበከል ይጠቀሳል፡፡
ሆኖም አፍሪካ ለዓለም ሙቀት መጨመር እና ለካርቦን ልቀት ችግር ድርሻዋ ኢምንት መሆኑን ያነሳው ዘገባው፥ በአንጻሩ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የምታስተናግደው ጉዳት ከፍተኛ ነውም ብሏል፡፡
ወሳኝ የሚባለው የጂኦስትራቴጂክ ቀጣናው የአፍሪካ ቀንድ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለከፋ ችግሮች ሲጋለጥ ቆይቷል፤ አሁንም እየተጋለጠ ነው፡፡
በዚህም እንደ በረሃማነት፣ የብዝሀ ህይወት መጥፋት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የመሬት መራቆት እና የጎጂ ነፍሳት መስፋፋት እየታየ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የምርት ወቅቶች የዝናብ እጥረት መከሰት በዚህም ዜጎች ለምግብና ውሃ እጥረት መጋለጥ፣ የወረርሽኝ በሽታዎች መጨመር፣ ድርቅ፣ ለዜጎች ስቃይና መፈናቅል፣ በከብቶች ህልውና ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ብቻ ሣይሆን በዚህ ሳቢያ የሚሞቱትም ቀላል እንዳልሆነም ነው የተነሳው፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከተል የሚችለውን አደጋ የተረዱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ 2019 አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ይፋ ማድረጋቸውን ዴይሊ ሳባህ በዘገባው አስነብቧል፡፡
ንቅናቄው በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያለመ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ የመትከል ታላቅ ዓላማ ያለው መርሐ-ግብር እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በመጀመሪያው ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአራት ቢሊየን በላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል፤ በአንድ ጀምበር ደግሞ ከ353 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን አስታውሶ ዘግቧል ዴይሊ ሳባህ፡፡
በዘንድሮው ንቅናቄ ደግሞ ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ይፋ መደረጉንም ጠቅሶ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመላ ሀገሪቱ ተተክለዋል ብሏል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እውን መሆን የሀገሪቱ የደን ሽፋን እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን፤ ለመርሐ ግብሩ መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ አድርጎ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገል በሀገሪቱ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲሳተፉ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ውህደት በማድረግ 1 ቢሊየን ችግኞችን ከስድስት ጎረቤቶቿ ጋር ተካፍላለች ነው ያለው ዘገባው፡፡
በበጋ ወቅት አርሶ አደሩን በማንቀሳቀስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመላ ሀገሪቱ መቀጠሉ ገልጾ፥ በዚህም በርካታ ሺህ ኪሎ ሜትር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መሰራቱም ተገልጿል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጥኖች እና የውሃ አያያዝ፥ ሥነ-ምህዳራዊ ስርዓቱን መደበኛ ለማድረግ፣ በረሃማነትን እና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል፣ እንዲሁም እንደ ዓባይ ባሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የውሃ ፍሰትን ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብሏል ዴይሊ ሳባህ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግብፅ እና ሱዳን ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ለኢትዮጵያ በገንዘብም ሆነ በሌሎች ድጋፍ ቢያደርጉ ይሻላቸዋል ሲልም ነው የዘገበው፡፡
ከዚህም በላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ተመድ እና የዓለም ማህበረሰብ እንዲህ ያሉ ለሌሎች አርዓያ የሆኑ መርሐ ግብሮችን በመደገፍ ሌሎች ፈለጉን እንዲከተሉ ማድረግ የጋራ ጥቅም እንደሚያመጣም ነው የገለጸው፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካባቢ መራቆትን በማሻሻል ካስመዘገበው ስኬት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት አፍሪካን አረንጓዴ ማልበስ ንቅናቄ ‘’አፍሪካን ግሪን ቤልት ኢኒሼቲቭ’’ን ከግብ ለማድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም መንግስት በፈረንጆቹ 2030 ዜሮ የካርቦን ልቀት ዓላማን እውን ለማድረግ በሙሉ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ ኃይልን ከውሃ፣ ንፋስ፣ ፀሀይ፣ ጂኦተርማል እና ከሌሎች ምንጮች እያገኘች ነው ብሏል የቱርኩ የዜና ምንጭ።
ሀገሪቱ የቀጣናዊ ውህደት ዋና አንቀሳቃሽ ሆናለች ሲልም፥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ኃይሏን በማጋራት ላይ እንደምትገኝ ጠቅሶ ከጂቡቲ፣ ሱዳንና ኬኒያ በተጨማሪ ከታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ጋር ለመስራት እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝም ጠቁሟል፡፡