አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ላይ ከአፀደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለእረፍት የተዘጉበት ወቅት ነው፡፡
ታዲያ ይህንን ከሁለት ወር ያላነሰ የእረፍት ጊዜ ልጆችዎ በምን እያሳለፉ ይገኛሉ ?
ልጆች የእረፍት ጊዜያቸውን ከቤታቸው ራቅ ብለው ወደሚገኙ ዘመዶች ጋር ለጥየቃ በመሄድ ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡
የሚሄዱበት አካባቢ ከሚኖሩበት አካባቢ ከራቀ (ክፍለ ሀገር) ከሆነ ደግሞ ከዘመዶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጠንከሩና ጥሩ ትዝታ ከመፍጠሩ ባለፈ የዚያን አካባቢ ባህል፣ ወግ እና እሴት የማየት የመማርና የማወቅ አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል፡፡
እንዲሁም ልጆች በቤታቸውና ከቤታቸው ሳይርቁ የክረምት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉም ይችላሉ፡፡
በዚህም ጊዜ ልጆች እንደየአቅማቸው ወላጆቻቸውን በማገዝ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጫወት፣ አስተማሪ እንዲሁም አዝናኝ ፊልሞችን በማየት (በወላጅ ምርጫ) እና መዝናኛ ስፍራዎች በመሄድ የሚያሳልፉበት ሁኔታ አለ።
በተጨማሪም ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትን ማለትም የሙዚቃ መሳሪያ፣ ስዕል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች፣ ውዝዋዜና ስፖርታዊ ክንውኖችን እንዲሁም ሌሎች ስልጠናዎችን በመውሰድ ያሳልፋሉ።
እንዲሁም ለሚቀጥለው የትምህርት ጊዜ የሚያግዛቸውን ማጠናከሪያ ትምህርት በመማር፣ መፅሐፍቶችን በማንበብ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ የሚጎበኙ ስፍራዎችንና ቴአትሮችን በማየት፣ የበጎአድራጎት ስራዎች ላይ መሳተፍ ማሳለፍ ሌላው የክረምት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ሊሆን ይችላል፡፡
በአንፃሩ ግን ያለ ወላጅ ፈቃድ እና እውቅና ከቤት ርቆ ሄዶ መጫወት፣ የመኪና መንገድ ላይ መጫወት፣ ከአቅማቸው በላይና ያልተፈቀደላቸውን ተግባራት ማከናወን፣ ረጅም ጊዜ ስክሪን ላይ ማሳለፍና ውሃ ወደሚያቁሩ ቦታዎችና ወደ ወንዝ በመሄድ ለመዋኘት መሞከር ተገቢ አለመሆኑንና ለአደጋ እንደሚያጋልጥ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ወላጆችም ልጆቻቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በፕሮግራም በአግባቡ እንዲጠቀሙና የክረምት ጊዜያቸው አይረሴ እንዲሆን የማድረግ እና የማገዝ ሃላፊነት አለባቸው፡፡
በፌቨን ቢሻው