አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሽኝት እየተደረገለት ይገኛል።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተሳታፊ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ206 ሀገራት የተወጣጡ (በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ጨምሮ) 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋና እና ቦክስ በ39 ስፖርተኞች እንደምትሳተፍ ኢዜአ ዘግቧል፡፡