Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን የመመለሱ ሒደት የተሳካ እንደነበር ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን የመመለሱ ሒደት የተሳካ እንደነበር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል መለሰ በለጠ ተናገሩ።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግ በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የጠለምት ወረዳ የማይጠብሪ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው በመመለስ ሥራ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለስ መቻላቸው ተገልጿል።

ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ተወካይ ሽማግሌዎች በጠለምት ሶስት ወረዳዎች ህዝቡን በማወያየት ተፈናቃዮችን የመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።

ህዝቡ ራሱ የመረጣቸው ተወካዮችን የማዋቀር ሥራ ከላይ እስከታች ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ከሰኔ 22 እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ስኬታማ ተፈናቃይ የመመለስ ሥራ መሰራቱን አስገንዝበዋል።

በዚህ መሰረትም የመከላከያ ሰራዊት የሁለቱን ክልሎች ስምምነት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት።

ትክክለኛ ተፈናቃዮችን የመለየቱ ሥራ በሁለቱም ወገን ሽማግሌዎች በመምረጥና በማደራጀት የአካባቢው ነዋሪነትን የሚያስረዳ መረጃ በማደራጀትና በመለየት የመመለስ ሥራው መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው አሁናዊ ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷በተለይም በማይጠብሪ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ሥራቸውን በአግባቡ እየከወኑ መሆናቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ቅኝት መረዳት ችሏል።

በታሪኩ ወ/ሰንበት

Exit mobile version