Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ28 በላይ ሀገራት የሚሳተፉበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዐውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከመስከረም 18 እስከ 24/2017 ዓ/ም ከ28 በላይ ሀገራት የሚሳተፉበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚቀርቡበት ዐውደ ርዕይ ሊካሄድ መሆኑን ገልጿል፡፡

ዐውደ ርዕዩ ሚኒስቴሩ ከደቡባዊ ትብብር ድርጅት ጋር በመተባበር የሚካሄድ ሲሆን ፥ ሚኒስቴሩ በሚዘጋጀው (ግሬት ሳውዘርን ፌር ፎር ኢንዶጂነስ ቴክኖሎጂ) ዐውደ ርዕይ ዙሪያ ለአባል ሀገራቱ አምባሳደሮች ማብራርያ ሰጥቷል።

በማብራሪያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በደቡብ ትብብር ድርጅት እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ዝግጅት ከተለያዪ አባል ሀገራት የተውጣጡት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች የሚሳተፉበትና ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ይሆናል ብለዋል።

የደቡብ ትብብር ድርጅት ዋና ፀሀፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሳላም በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በመደገፍ ከቴክኖሎጂ ገዢዎችና ተጠቃሚዎች በተጨማሪ የኢንዱስትሪ አብዮት ፈጣሪዎችና ቴክኖሎጂ አምራቾች መሆን ይገባናል።

ዐውደ ርዕዩ ከመስከረም 18 እስከ 24/2017 ዓ/ም የሚካሄድ ሲሆን ÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ28 አባል ሀገራት የተመረጡ ኢንዶጂነስ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበትና የሚበረታቱበት ዐውደ ርዕይ ነው።

ዐውደ ርዕዩ ከ28 በላይ ሀገራትና ተባባሪ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ሆኖ ፤ ከእያንዳንዱ አባል ሀገር ቢያንስ ሦስት የኢንዶጅነስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚቀርቡበትና በአጠቃላይ ከ100 በላይ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለእይታ የሚበቁበት መሆኑም ተመላክቷል።

በዝግጅቱ የደቡብ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የሚገኙበት እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

በዚህም የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የግል ተመራማሪዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ለሀገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version