ዓለምአቀፋዊ ዜና

ከአንድሮይድ አንጻር የአይፎን ስልኮች የመጠለፍ ዕድል ዝቅተኛ ነው – ጥናት

By Mikias Ayele

July 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአንድሮይድ አንጻር አይፎን ስልኮች የመጠለፍ ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ሴል ብራይት የተሰኘ የእስራኤል ዲጂታል ኢንተለጀንስ ኩባንያ ጥናት ውጤት አመላከተ፡፡

የአሜሪካ ፀጥታ እና ደኅንነት ተቋም (ኤፍ ቢ አይ) በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገውን ቶማስ ማቲው አድራሻ ማግኘቱን ተከትሎ የተንቀሳቃሽ ስልኮች በቀላሉ መጠለፍ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በስልክ ጠለፋ ምክንያት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ምስጢርና ግላዊ ጉዳይ አደጋ ላይ ወድቋል እየተባለ ነው፡፡

በስልኮች ላይ የመረጃ ጠለፋ እየተበራከተ መመጣቱን የገለጸው ኩባንያው÷ ከመጋቢት 2024 ጀምሮ የአይፎን ስልኮችን መጥለፍ አልተቻለም ብሏል፡፡

ለዚህም የአይፎን ስልኮች ስሪት በቀላሉ እንዳይጠለፉ አድርጓል ማለቱን አር ቲ ዘግቧል፡፡

በአንጻሩ ጎግል ፒክስል 6፣ 7 ወይም 8 ከተሰኙት ስማርት ስልኮች ውጭ ሌሎች አንድሮይድ ስልኮች በቀላሉ ለጠላፊዎች የተጋለጡ ናቸው ብሏል፡፡

እየተበራከተ የመጣውን የስልክ ጠለፋ ለመከላከልም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና የንግድ ሰዎች በእስራኤሉ ሴልብራይት ኢንተለጀንስ ኩባንያ ስልካቸው እንዳይጠለፍ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡