ስፓርት

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን አበረታቱ

By Shambel Mihret

July 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ልምምድ በሚያደርጉበት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመገኘት ጎብኝተዋል፡፡

ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚታወቁት በዓለም አደባባይ መድረክ በአሸናፊነት ነው፡፡

ስለሆነም በኦሎምፒኩ የምትሳተፉ አትሌቶች በአሸናፊነትና በጀግንንነት ታሪክ መስራት እንደምችሉ እናምንባችኋለን ብለዋል።

እንደ ትላንቱ ዛሬም በድልና በስኬት ተመልሳችሁ ሕዝባችሁን የምታኮሩ ያድርጋችሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

አትሌቶች የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ትልቁን ሚና እንደሚይዙ አንስተው÷ኢትዮጵያ በምትታወቅበት በቡድን ስራ እና በስፖርታዊ ጨዋነት እንደምታኮሩን እተማመናለሁ ብለዋል፡፡

በኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ስለ ቅድመ ዝግጅታቸው እና ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ከሚኒስትሯ ጋር መወያየታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡