Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ 6ኛ ዙር 3ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩም የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የሐረሪ ጉባዔ ፣የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የ2016 ዓመት የሥራ አፈፃፀማቸውን በጉባዔው ላይ አቅርበዋል።

በጉባዔው ላይ በበጀት ዓመቱ በክልሉ በባህል፣ ቅርስና በሐረሪ ቋንቋ ጥበቃና የማጎልበት ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸው ተመላክቷል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት÷ በ2016 ዓመት የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃን በማጎልበት የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በተለይ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የሸዋል ዒድ በማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ እና የሐረሪ ቋንቋን ከማሳደግና ደረጃን ከማሻሻል አንፃር የተዘጋጁ የትርጉም መተግበሪያዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ጉባዔው ከመከረ በኋላ በሙሉ ድምፅ የጸደቁ ሲሆን÷ የ2017 ዓመት የሐረሪ ጉባዔ ፣ የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ዕቅድ ቀርቦ በአባላቱ አስተያየት ከተሰጠባቸው በኋላ በሙሉ ድምፅ መፅደቃቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version