Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

እስራኤል በሁቲ አማጺያን ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሰሜናዊ የመን በሚንቀሳቀሱ የሁቲ አማጺያን ላይ የተቀናጀ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች፡፡

ጥቃቱ አማጺያኑ ቀደም ሲል በቴል-አቪቭ የፈጸሙትን የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተከትሎ የተወሰደ አጸፋዊ እርምጃ ነው ተብሏል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት÷ የእስራኤል የአየር ሃይል ሁቲዎች በተቆጣጠሩት የሁዴይዳህ ወደብ አካባቢ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ለአማጺያኑ ግልጽ መልዕክት አስተላልፈናል ብለዋል፡፡

የሁቲ ቡድኖች አባል የሆነው ሞሃመድ አቡዱሰላም በበኩሉ÷እስራኤል በቀይ ባሕር አካባቢ በምትገኘው ሁዴይዳህ ወደብ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጧል፡፡

ጥቃቱ ሁቲዎች ለፍልሰጤም የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማስቆም ያለመ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡

እንደ ሁቲዎች የዜና አውታር ዘገባ በጥቃቱ ሶስት ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን÷ከ80 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

እስራኤል ባለፉት ወራት ከአማጺያኑ የተተኮሱ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ግዛቷ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸማቸውን ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል፡፡

አሁን ላይ በአማጺያኑ ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃትም የመጀመሪያ አጸፋዊ ምላሽ  እንደሆነ መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version