አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በጎንደር ከተማ የፋሲል-አብያተ መንግስት የጥገና ስራ ያለበትን ሁኔታ ጎበኙ።
በጉብኝቱ የከተማው ከንቲባ ባዩህ አቡሀይን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች፣ ከከተማው የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
በተያያዘ የመገጭ ግድብን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የጎንደር የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ለአዲስ ተቋራጭ ተሰጥቷል ብለዋል።
ለአዲስ ኮንትራክተር ቅድሚያ ክፍያ ተሰጥቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት በማጠናቀቅ የጎንደርን የንፅህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የመገጭ ግድብ አማካሪ መሃንዲስ ወርቅነህ አሰፋ በበኩላቸው የግድቡ 57 በመቶ ላይ ሲሆን በቀጣይ ሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።