አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ውጭ ጉዳይ እና መከላከያ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን ሀገራቸው በኢትዮጵያ ለልማትና ለሰብአዊ ፕሮግራሞች የሚውል የ15 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓን ገለጹ።
ሚሼል ማርቲን በአፍሪካ ቀንድ ያካሄዱትን የአራት ቀናት የስራ ጉብኝት ማጠቃለያ በአዲስ አበባ አድርገዋል።
በዛሬው ዕለት ከገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ጋር በነበራቸው ውይይት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ተጠቃሚ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ባለፉት 50 ዓመታት አየርላንድ አገልግሎት-መር እና ወጪ ንግድ ላይ ትኩረት ያደረገ የኢኮኖሚ መንገድ መከተሏን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በምታደርገው የልማት ጉዞ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው÷ ሀገራቸው ለችግር የተጋለጡትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።
ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር የተወያዩት ሚሼል ማርቲን÷ የአየርላንድ የዜጎች ምክር ቤት እና የሰላም ግንባታ ልምድ አካፍለዋል።
ሰላም ግንባታና እርቅ ረጅም መንገድ ይወስዳል ያሉ ሲሆን÷ አንዳችን ከሌላችን ልንማር የምንችለው ብዙ ነገር አለ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአመቱ መጨረሻም የኮሚሽኑን አባላት በአየርላንድ ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን መግለፃቸውን ከአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡