የሀገር ውስጥ ዜና

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናወነ

By Tamrat Bishaw

July 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ “የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ተሳትፎ በማድረግ የችግኝ ተከላ አካሄደ።

በመርሐ ግብሩም የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤት አባላት፣ የጽሕፈት ቤቱ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ መርሐ ግብሩን ማስጀመራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የችግኝ ተከላው የተካሄደው በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ከአራት ኪሎ እስከ መገናኛ ባለው የኮሪደር ልማት፣ አዲስ በተዘጋጀው የቀበና አረንጓዴ አካባቢ ሲሆን÷ በዕለቱም 3 ሺህ 600 ያህል ችግኞች ተተክለዋል።

ምክር ቤቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ተሳትፎ በማድረግ የችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።