የሀገር ውስጥ ዜና

አራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል ተስማሙ

By Meseret Awoke

July 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በጋራ የእንስሳት በሽታ ቅኝት ማድረግ፣ ክትባት መስጠትና መረጃ መለዋወጥ የሚያስችላቸው መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስታውቋል።

የትብብር ስራው ሀራቱን ባቀፈው የካራሞጃ ድንበር ተሻጋሪ የልማት ትብብር መሰረት የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከልና ሕገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ለመቆጣጠር አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

የቅድመ ቅኝት ስራው የእንስሳትን የበሽታ ተጋላጭነት የመቀነስ እንዲሁም በምግብና በአኗኗር ሁኔታ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ የማስቀረት ዓላማ እንዳለተመላክቷል።

በድንበር አካባቢ የሚከሰት የእንስሳት በሽታን አስመልክቶ የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ በሽታው ሳይዛመት ጊዜውን የጠበቀና ውጤታማ የጋራ ውሳኔን ለማሳለፍ እንደሚያግዝ ነው የተጠቆመው።

የበሽታው አዝማሚያን አስመልክቶ የሚሰራጩ ትክክለኛና ተዓማኒ መረጃዎች የቁም እንስሳት ንግድ የተሳለጠ እንዲሆንና በነጋዴዎች መካከል ያለውን መተማመን ለመጨመር እንደሚያስችል መጠቀሱንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡