Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለተሿሚ አምባሳደሮች እየተሠጠ ያለው ሥልጠና ውጤት ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራን እንዲከውኑ የሚያግዝ ነው – አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች እየተሠጠ ያለው ሥልጠና ውጤት ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራ መከወን እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዴዔታዋ ዛሬ በአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ሥልጠና ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ፥ የሥልጠናው ይዘቶች ከ24 በላይ በሆኑ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

አሁን እየተሰጠ ያለው የቅድመ ሥምሪት ስልጠና ንድፈ ሃሳባዊ ብቻ ሳይሆን የተግባር ስራን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

የአምባሳደርነት አመራርና ሃላፊነቶች ዙሪያ፣ በአጠቃላይ ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት አዝማሚያዎች እና የመጪው ጊዜ የዲፕሎማሲ አካሄዶች ላይ ስልጠናው መሰጠቱን ቀጥሏል ብለዋል።

በዘርፉ የላቀ ክህሎትና የአመራርነት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችና የሥራ ሃላፊዎች በአሰልጣኝነት እየተሳተፉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለ24 ዲፕሎማቶች የአምባሳደርነት ሹመት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

Exit mobile version