አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኩፍኝ ማለት ሚዝልስ (Measles) በተባለ ረቂቅ ተህዋስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ የሆነ በሽታ ነው።
በአብዛኛው ክትባት ያልወሰዱ ህፃናት ላይ የሚከሰት ቢሆንም አዋቂዎች ላይም ሊከሰት ይችላል።
የኩፍኝ በሽታ በዋናነት በትንፋሽ የሚተላለፍ ሲሆን÷ ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎችም በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም፣ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ንክኪ መኖር፣ የምግብ እጥረት እና የቫይታሚን ኤ እጥረት ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ፡፡
የኩፍኝ በሽታ ዋና ዋና ምልክቶች ከፍተኛ የሆነ ሙቀት፣ ዐይን መቅላት፣ ማሳል፣ ውሃ የመሰለ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ከራስ/ አንገት አካባቢ ጀምሮ ወደ እግር የሚሄድ ሽፍታ፣ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እንዲሁም ተቅማጥና ማስመለስ ናቸው፡፡
እነዚህን ምልክቶች ከተመለከቱ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባ ይመከራል፡፡
በኩፍኝ በሽታ ሊመጡ የሚችሉ ውስብስብ ችግሮች ምንድናቸው?
የሳንባ ምች፣ የጆሮ ክፍል በሽታ፣ ዐይነ ስውርነት፣ የጉበት በሽታ እና የመድማት ችግር መሆናቸውን ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኩፍኝ ክትባት ልጆች በወቅቱ እንዲወስዱ ማድረግ፣ የግል እና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ፣ በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እና በበሽታው ከተጠቁ ወይም የኩፍኝ ምልክቶች ከታዩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል፡፡