የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 310 ኪ.ግ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገባ

By Meseret Awoke

July 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 310 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱ ተገለጸ፡፡

በክልሉ የተቋቋመው የማዕድን ኮማንድ ፖስት ባለፉት 12 ወራት በማዕድን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን የገመገመ ሲሆን÷በመድረኩ በ12ወራት ውስጥ 310ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱ ተገልጿል።

በዚህም በርካታ አዳዲስ ወርቅ አምራች ማህበራት ፍቃድ ወስደው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን ፥ ለ2 ሺህ 404 ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑም ተጠቅሷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና እና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ተንኩዌይ ጆክ ፥ ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የማዕድን ዘርፉ ላይ እየተደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል አበረታች እንደነበር ገልፀዋል።

ክልሉ ካለው የወርቅ ሃብት አኳያ ግን ወደ ብሔራዊ ባንክ እየገባ ያለው መጠን እየተሻሻለ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ነው የገለጹት።

በመሆኑም በቀጣይ ህገ ወጥ ዝውውርን በመቆጣጠርና ሕጋዊ የሆኑ አምራቾችን በማገዝ መጠኑን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ሀላፊ ወ/ሮ አኳታ ቻም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፥ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ ምርት ለማሳደግ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን እያሰፋን ነው።

በመሆኑም የሚስተዋሉትን ሕገ-ወጥ ተግባራት ለማስቀረት ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር በመናበብ እንደሚሰራ መናገራቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡