የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮ ቴሌኮም እስከ ሐምሌ 30 ድረስ ግማሽ ሚሊየን ችግኝ እንደሚተክል አስታወቀ

By Meseret Awoke

July 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ግማሽ ሚሊየን ችግኝ በመላ ኢትዮጵያ እንደሚተክል የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬ-ህይወት ታምሩ ገለጹ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም አመራሮችና ሰራተኞች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡

በተቋም ደረጃ “ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ ” በሚል እየተካሄደ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ የተሳተፉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፥ ተቋሙ ከመደበኛ ስራው ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትኩረት በመስጠት ለተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገኝበት ገልፀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት አምስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኝ በመትከል የመንከባከብ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዚያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ነው የገለፁት።

በዚህ ዓመትም እስከ ሐምሌ 30 ድረስ ግመሽ ሚሊየን ችግኝ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ እንደሚተከል ገልጸው፥ በዚህም ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞች በተከላ መርሐ ግብሩ እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም ጊዜያዊ የስራ ዕድል ይፈጠራል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።

በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ አምስት ስፍራዎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የተቋሙ ሰራተኞች የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አከናውነዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ