አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍን መፈረሟ የኢትዮጵያ ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን የሚያመላክት ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
‘የኢትዮጵያ እና የግብፅ ሽኩቻ’ የሚል መጽሐፍ የጻፉት ውብሸት ሲሳይ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፥ በናይል ውሃ ጉዳይ ላይ በግብፅ እና ሱዳን ተይዞ የነበረውን የበላይነት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ እየቀለበሰች መምጣቷን ያሳያል።
የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ግዛቸው አማረ (ዶ/ር)፥ የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ መጠናከሩን እና የምታነሳቸው ሀሳቦች ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሀገራት የናይል የትብብር ማዕቀፍን መፈረማቸው ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ የሚነሱ ክርክሮችን እንድታሸንፍ እንደሚያስችላትም ነው ምሁራኑ የጠቀሱት።
የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በርካታ ስራዎችን ስታከናውን የቆየች ሲሆን፤ በተለይም ሀገራትን በማስተባበር ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ያከናወነቻቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸው ተገልጿል።
የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የቀጣናው ሀገራት በኃይል በመተሳሰር የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
በአልማዝ መኮንን