ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያና ቻይና የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀመሩ

By Tamrat Bishaw

July 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር ወታደራዊ ልምምድ መጀመራቸውን የሩሲያ እና የቻይና መንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ሀገራቱ አሜሪካ በሁለቱም ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ተከትሎ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወታደራዊ እና የንግድ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።

‘የባህር ላይ ትብብር – 2024’ በሚል የተሰየመው የሩስያ-ቻይና የባህር ኃይል ልምምድ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በቻይና ዣንጂያንግ ወደብ መካሄዱን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም ገጹ ባሰፈረው መልእክት ገልጿል።

የሀገራቱ የባህር ኃይል መርከቦች ከቻይና የባህር ኃይል ፀረ-ሰርጓጅ አቪዬሽን ጋር በመሆን የአየር መከላከያ ልምምዶችን እና ፀረ-ሰርጓጅ ልምምድ ማካሄዳቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አክሎ ገልጿል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ልምምድ ሀገራቱ እያንዳንዳቸው ቢያንስ ሶስት መርከቦችን ማሰማራታቸውን የቻይናው ግሎባል ታይምስ ጋዜጣ የቻይናን ባህር ኃይል ጠቅሶ ዘግቧል።

የሩሲያ መንግስት መገናኛ ብዙሃን የሀገራቱ የባህር ኃይሎች የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አንድ አካል የሆነውን የመድፍ ተኩስ ልምምድ ማድረጋቸውን ዘግቧል፡፡

የጋራ ልምምዱ የተጀመረው በሰላማዊ ውቅያኖስ ሰሜናዊ ክፍል ሀገራቱ በተናጠል ሲያደርጉት የነበረውን የቁጥጥር ሥራ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

የቻይና እና የሩሲያ የጋራ እንቅስቃሴ በመካከላቸው በብዙ አቅጣጫ ያለውን በተግባር የተደገፈ ጥልቅ ትብብር እንደሚያሳይም ነው የተመላከተው፡፡

ልምምዱ በሁለቱ ሀገራት ላይ ሊፈጠር የሚችል የባህር ላይ የደህንነት ስጋትን በጋራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ተጠቁሟል፡፡