አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የክልሎች እና የከተማ አስተዳደር አጀንዳ አሰባሰብ ምዕራፍ በሶስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚያከናወን አስታውቋል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት በተመሳሳይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር የሚካሄድባቸው ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውን ኮሚሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) የተሳታፊ ልየታው በ10 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች አስቀድሞ መጠናቀቁን አስታውሰዋል።
በቀሪዎቹ ክልሎች ከነሀሴ 30 በፊት የአጀንዳ ልየታው እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው፤ የአፋር ክልል ወደ መስከረም ሊያልፍ እንደሚችል አመልክተዋል።
በትግራይ እና በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታውን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ