ግለሰቦቹ ሲያዘዋውሩት የተያዘው የአፈር ማዳበሪያ ተሽጦ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ታዟል።
የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ህግ ሽመልስ አስረዲን፣ ብናልፈው በላይ፣ ልመንህ ክብረት፣ ኤልያስ ለማና ሹራ ሀይሉ የተባሉ ግለሰቦች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ የሙስና አዋጅ ቁጥር አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በአራት መዝገብ ከፋፍሎ ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህም ሽመልስ አስረዲን በተባለው ግለሰብ ላይ በቀረበ የክስ መዝገብ እንደተመላከተው የዋጋ ግምቱ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ 450 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተሽከርካሪ በመጫን በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የወጪ ደረሰኝ ሰነዶችን በመጠቀም መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ አማራ ክልል በማጓጓዝ ላይ እያለ በሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ዲዳ ሄጦ በተባለ ቦታ ላይ በፀጥታ አካላት ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በ2ኛ መዝገብ ብናልፍ በላይ የተባለ ተከሳሽ ደግሞ 432 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተሽከርካሪ በመጫን በግብርና ኮርፖሬሽን ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የወጪና ሌሎች ሰነዶችን በመያዝ መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ አማራ ክልል ሲያጓጉዝ በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ በኩሪ ቀበሌ መንደር 8 ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ በፀጥታ አካላት መያዙ ተጠቅሶ ተከሷል፡፡
በ3ኛ መዝገብ ልመንህ ክብረት ተዋበ የተባለ ተከሳሽ 60 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተሽከርካሪ ጭኖ በጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ላይ እያለ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ በፍቼ ከተማ ዲዳ ሄጦ በተባለ አካባቢ በፀጥታ አካላት መያዙ ተጠቅሶ ክስ ቀርቧል።
በ4ኛ ክስ መዝገብ ማዳበሪያ ሽያጭ የመጋዘን ኃላፊ ኤልያስ ለማ እና የሰሜን ሸዋ ዞን የጂዳ ወረዳ ደበሊ ገንጆ ቀበሌ የመሰረታዊ ቁጠባ ህብረት ስራ ሽያጭ ሰራተኛ ሹሪ ሀይሉ ላይ በቀረበው ክስ ደግሞ የሙስና አዋጁን አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በህገወጥ መንገድ 22 ኩንታል ማዳበሪያ ሲያዘዋውሩ በፀጥታ አካላት መያዛቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
ባጠቃላይ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ክስ ዝርዝርና ማስረጃዎችን የግራ ቀኝ ክርክሮችን መርምሮ የወንጀል ተግባሩ መፈጸሙን በማረጋገጥ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ በማስተላለፍ በየደረጃው ከ3 ዓመት ከ7 ወር እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ