Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ተባለ 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ገለፁ።

አምባሳደር አክሊሉ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን÷ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሎጂስቲክስ እድሎች አማራጮችና ማበረታቻዎች ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር አክሊሉ ከበደ በበኩላቸው÷ ኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በየአህጉሩ የተከፋፈለ ዴስክ በማዋቀር ጭምር የሚያደርገው እንቅስቃሴና የሚሰጠው ቀልጣፋ አገልግሎት ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ማደግ ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ልዑካን ቡድኑ በቆይታው ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ከተሰማራው የአርማዳ ግሩፕ ባለቤትና የማኔጅመንት አባላት ጋር በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም በሪልስቴት ዘርፍ እንዲሰማራ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ማድረጉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version