አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከደረጃ በታች በሚያመርቱ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ከደረጃ በታች የፌስታል ምርት ሲያመርቱ ከተገኙ ድርጅቶች መካከልም÷ ኤል.ኤች ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ ኤ.ኤች ስማርት ፕላስቲክ ማምረቻ፣ ኢለኒ ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ሪም ፕላስቲክ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር፣ ኤስ. ኤስ. ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ወይንሸት፣ ሳራና ጓደኞቻቸው ፕላስቲክ መልሶ መጠቀም ሽርክና ማኅበር፣ አግማስ ማኑፋክቸሪንግ እና ዘቢባ ፕላስቲክ ማምረቻ እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ በወጣው አዋጅ ቁጥር 513/1999 መሰረትም 0 ነጥብ 03 ሚሊ ሜትር እና ከ0 ነጥብ 03 ሚሊ ሜትር በታች የሆኑ ከአፈር ጋር መዋሃድ የማይችሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረትም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የተከለከለ መሆኑን ያስታወሰው ባለስልጣኑ÷ ዛሬ የተወሰደው ርምጃም ይህን መነሻ ያደረገ ነው ብሏል፡፡
በቀጣይም ከደረጃ በታች በሚያመርቱ የፕላስቲክ ማምረቻ ድርጅቶች ላይ የተጠናከረ ርምጃ እንደሚወሰድ ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ አረጋግጧል፡፡