አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን ከቻይና ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ እንደምታጠናክር ተመራጩ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ገልጸዋል።
በቅርብ በታተመ መጣጥፋቸው ቻይና ከሩሲያ ጋር በመሆን በአስቸጋሪ ጊዜያት ከኢራን ጎን መቆሟን ያነሱት ፔዜሽኪያን÷ ይህንን ወዳጅነት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡
“መልእክቴ ለአዲሱ ዓለም” የተሰኘው መጣጥፋቸውም በኢራን ዴይሊ ቴህራን ታይምስ የእንግሊዘኛ ዕትም መታተሙ ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 2021 በኢራን እና በቻይና መካከል የተፈረመውን የረዥም ጊዜ አጠቃላይ የትብብር ስምምነት በመጥቀስም÷ ከቻይና ጋር ያለን የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመስረት ትልቅ ምእራፍ ነው ብለዋል።
ወደ አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት በምናደርገው ሽግግርም ከቤጂንግ ጋር ሰፊ ትብብር ለማድረግ እንጠብቃለን በማለት ገልፀዋል።
በ2023 ቻይና በቴህራን እና በሪያድ መካከል ለሰባት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈታ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቷንም አንስተዋል፡፡
ቻይና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላትን ገንቢ ራዕይ እና የአርቆ አሳቢነት አቀራረብም አሞካሽተዋል።
አስተዳደራቸው÷ ሀገራቸው ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሚዛናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ከሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም፣ ኢኮኖሚያዊ ልማት ፣ ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላም እና ደህንነት መስፈርቶች ጋር በማጣጣም “በዕድል ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ” እንደሚከተልም ቃል ገብተዋል።
“ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ቅድሚያ እንሰጣለን” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
አስተዳደራቸው በዓለም ደቡብ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ተዋንያኖች፤ በተለይም ከአፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ግንኙነት መፍጠርን ያካተተ የውጭ ፖሊሲ እንደሚከተሉም ተናግረዋል።