ስፓርት

የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይካሄዳል

By Melaku Gedif

July 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እና እንግሊዝ ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በጀርመን አስተናጋጅነት ከሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ሥነ- ሥርዓት በዛሬው ዕለት ይካሄዳል፡፡

በዚህ መሰረትም ለፍጻሜ ጨዋታ የደረሱት ስፔንና እንግሊዝ የአህጉሩን የክብር ዋንጫ ለማንሳት ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይፋለማሉ፡፡

በግማሽ ፍጻሜው እንግሊዝ ኔዘርላንድስን እንዲሁም ስፔን ፈረንሳይን በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የደረሱት፡፡

በበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም በሚካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን ለ4ኛ ጊዜ በማንሳት ደረጃዋን ለማሻሻል ከባድ ፉክክር ታደርጋለች፡፡

በሌላ በኩል እንግሊዝ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት የምታደርገው ፍልሚያ በእግር ኳስ ተመልካቹ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ስፔንና እንግሊዝ በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን÷በታሪካቸው ደግሞ ለ27 ጊዜያት ያህል እርስ በርስ ተገናኝተዋል፡፡

በዚህም እንግሊዝ 14ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ስፔን ደግሞ 10 ጊዜ አሸንፋለች፤ ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታወች ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት የፍጻሜ ጨዋታን በጥንቃቄ በመጫወት ዋንጫውን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሉዊስ ዴ ላፉንቴ በበኩላቸው ÷ የፍጻሜ ጨዋታው ከባድ ፉክክር እንደሚደርግበት ጠቁመው ፤ ቡድናቸው ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታል ብለዋል፡፡

በስፔን በኩል አነጋጋሪው የ17 ዓመቱ ኮከብ ላሚን ያማል እንዲሁም የ30 ዓመቱ የእንግሊዝ አጥቂ ሃሪ ኬን በጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ተጠባቂ የፍጻሜ ፍልሚያ የ35 ዓመቱ ፈረንሳዊ ፍራንስዋ ሌቲክሲየር በዋና ዳኝነት ይመራሉ።