Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በክልሎችና በድሬዳዋ የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ እና በክልሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

በሒደቱም እስካሁን የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ የተጀመረ ሲሆን ፥ በአዲስ አበባ የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁ ይታወቃል።

በቀጣይ በድሬዳዋና በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው፡፡

በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የተሳተፉ ዜጎች ለሀገር ይበጃል ያሉትን የመፍትሔ ሃሳብ በነፃነት በማቅረባቸው በሒደቱ ላይ ግልጸኝነት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሒደቱ ግልጸኝነት የተፈጠረበትና ህብረተሰቡንም ማስገንዘብ የተቻለበት እንደሆነ ነው ያስረዱት።

ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ በድሬዳዋ እና በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ጥናት በማካሄድ ቀጣይ የምክክር ምዕራፍ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል ብለዋል።

በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች በምክክር የጋራ ሀገራዊ መፍትሔ ለመሻት እንዘጋጅ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክር ሒደቱ እስካሁን ህብረተሰቡ ላሳየው ድጋፍና በጎ አመለካከት ኮሚሽነሩ ምስጋና ማቅረባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version