አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠራዊቱን ኑሮ በሁለንተናዊ መልኩ የተሻለ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ፡፡
ጄኔራል አበባው በምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል ተሰማርቶ ሀገራዊ ግዳጁን እየፈፀመ ለሚገኘው ኮር የተሠራውን የመኖሪያ ቤት ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም፤ የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ በመላው ሀገሪቱ ለሠራዊቱ ጊዜያዊ መጠለያ ቤቶችንና ቋሚ መኖሪያ ካምፖችን በመገንባት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የመሀንዲስ ዋና መምሪያ በውጊያ ምህንድስናም ይሁን በቤቶች ግንባታ፣ በመንገድና በከርሰ ምድር ውሃ ማውጣት ስራ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ቤቶቹ በአጭር ጊዜ ተገንብተው እንዲጠናቀቁና ለተፈለገው አላማ እንዲደርሱ የምስራቅ ዕዝ አካል የሆነው አንድ ኮር ከጥበቃ ስራው ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደተወጣ መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡