የሀገር ውስጥ ዜና

በሐረር ከተማ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

July 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ተግባራት የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ መሆናቸውን የከተማዋ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ኤልያስ ዮኒስ÷ ከተማዋን የማስዋብ ስራ የተጀመረው በ2015 ዓ.ም የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን በመንከባከብ መሆኑን አስታውሰዋል።

ቅርሱ የሚገኝበትን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የማስዋብና ሌሎች ስራዎች በተቋማትና በሌሎች ባለድርሻ አካላት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማው እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት ስራዎች ሐረርን ውብ፣ ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹና ተስማሚ እንድትሆን አስችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም በከተማዋ እየተሰራ ያለው ጌጠኛ የእግረኛ መንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችና ሌሎችም የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ መሆኑን አንስተዋል።