የሀገር ውስጥ ዜና

116 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

By Melaku Gedif

July 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት 116 አዳዲስ የገጠር ከተሞች እና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በኩል በርካታ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 100 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 116 የገጠር ከተሞች እና መንደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ የሃይል አማራጭ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ 2 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለዚህም 1 ሺህ 160 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር፣ 1 ሺህ 588 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እና 382 የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡