Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በጀርመን ከተከለች ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በጀርመን የምትተክል ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወሰድ ሩሲያ አስጠነቀቀች፡፡

አሜሪካ ዘመናዊ የተባሉ ሚሳኤሎችን በፈረንጆቹ ከ2026 ጀምሮ በጀርመን እንደምትተክል ውሳኔ ያሳለፈችው በ75ኛው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ጉባኤ ላይ ነው፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የሩሲያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰረጌ ርያብኮቨ እንዳሉት ÷አሜሪካ አዲስ ለደቀነችው ስጋት ሞስኮ ወታደራዊ ምላሽ ትሰጣለች፡፡

የሚሳኤሎቹ መተከል አሜሪካ ለኔቶ ያላትን አጋርነት ሚያመለክትና የአውሮፓን የተቀናጀ የመከላከል ሥርዓትን ማጠናከር ያለመ ነው ሲሉ አሜሪካና ጀርመን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የጀርመኑ የመከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒሰቶሪስ ÷በጊዜያዊነት የሚተከሉት የአሜሪካ መሳሪያዎች የኔቶ አባል ሀገራት እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጊዜ የሚሰጥ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከክሬምሊን የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የአሜሪካ ውሳኔ እጅግ አደገኛና ምላሽ የሚያስፈልገው ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version