ቴክ

ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን በመሰረተ ልማት ለማብቃት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ተባለ

By Shambel Mihret

July 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን በመሰረተ ልማት በማሻሻልና በማብቃት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ትብብር ኃላፊ ሮቤርቶ ሺሊሮ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራበትን የዲጂታል ስትራቴጂ እና የመንግሥት ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር የጥናት ሰነድ የማጠቃለያ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ በማጎልበት ዓለም የደረሰበት እድገት ላይ ለመድረስ የዲጂታል ስትራቴጂው ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ ስራዎችን በመስራት የኢኮኖሚ ምህዋሩን በፍጥነት መዘወር ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ላላት ኢትዮጵያ ሰነዱ ራዕይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ አለም አቀፋዊ ምርጥ ልምዶችን ያካተተ እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን የሚመሩ ቁልፍ መርሆችን መሰረት ያደረገ የዲጂታል ስትራቴጂ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ትብብር ኃላፊ ሮቤርቶ ሺሊሮ÷ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ በዲጂታል፣ በሃይል እና በትራንስፖርት ዘርፎች ግልፅና ደህንነቱ የተጠበቀ አውታርን ለማሳደግና የጤና፣ የትምህርት እና የምርምር ስርዓቶችን በዓለም ዙሪያ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን በመሰረተ ልማት በማሻሻልና በማብቃት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኤሌክትሮኒክ መንግስት አገልግሎት ስትራቴጂና ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር 2024 – 2029 ሰነድ በቀጣይ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ብሄራዊ ካውንስል ቀርቦ እንደሚፀድቅና ወደ ሙከራ ትግበራ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡