Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቻይና ለኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ሊቀመንበር ሉዎ ቻውሁይ ጋር በቤጂንግ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው አቶ መላኩ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ የኢኮኖሚ ስኬቶችን ማስመዘገቧን እና በሀገሪቱ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁም የቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ሉዎ ቻውሁይ በበኩላቸው÷ተቋማቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚያደርገውን ድጋፋ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፉን ለማጠናከር የቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማገዝ ኤጀንሲው በኢትዮጵያ በርካታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እንዳደረገም ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version