የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ነው

By Amele Demsew

July 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በመመረቅ ላይ ናቸው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል፡፡

መሰረተ ልማቶቹ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ግንባታቸው በከተማ አስተዳደሩ ሲካሄድ ከቆዩት 70 ፕሮጀክቶች መካከል 68ቱ ተጠናቀው በዛሬው እለት ለምረቃ መብቃታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ዛሬ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ሌሎች የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንደሚገኙበት ተመላክቷል ።

በተመሰሳይ በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በ81 ሚሊየን ብር የተገነባ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እና ሌሎች የከተማው የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተስፋዬ እጅጉ