አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2030 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን ለምታደርገው ጉዞ የመንገድ መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
ሁለተኛውን ምዕራፍ የገጠር መንገዶች ትስስር ፕሮግራም ይፋ ባደረጉበት ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የገጠር መንገዶችን ከዋና መንገዶች ጋር ማስተሳሰር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አለው።
ፕሮግራሙ በገጠር የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት የተደረገበት በመሆኑ ወደ 407 ሚሊየን ዶላርበጀት የተመደበለት መሆኑን ጠቁመዋል።
300 ሚሊየን ዶላር ከዓለም ባንክ 107 ሚሊየን ዶላር ደግሞ ከክልሎች የተገኘ ነው ብለዋል።
በ12 ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ126 ወረዳዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ስራው ይከናወናል ተብሏል።
ከ7 ሺህ 500 በላይ አዲስ የጠጠር መንገድ የሚገነባ ሲሆን 10 ሺህ 71 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና ይደረጋል።
በተጨማሪም ከ10 ሺህ በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚሰሩም ተመላክቷል።
ከአዳዲስ የመንገድ ግንባታ ባለፈ ከዚህ ቀደም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ መንገዶችን የማጠናቀቅ ስራ የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል፡፡
በታሪኩ ለገሰ