ስፓርት

የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኦሊቪየ ዢሩ ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን አገለለ

By Mikias Ayele

July 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኦሊቪየ ዢሩ በ37 ዓመቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡

ዢሩ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ትናንት ምሽት ሀገሩ ፈረንሳይ ከስፔን ጋር ጨዋታዋን ስታደርግ ተቀይሮ በመግባት የተጫወተ ሲሆን በሽንፈት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ በይፋ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ አግልሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2011 የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ማድረግ የቻለው ዢሩ 137 ጊዜ ለሀገሩ በመሰለፍ 57 ግቦችን በማስቆጠር የቀድሞውን የፈረንሳይ ኮከብ ቴሪ ሄንሪ ክብረ ወሰንን በማሻሻል የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችሏል፡፡

የፈረንሳዩ አሰልጣኝ ዲዲየ ዴሾ “የዢሩን ጫማ መስቀል መስማት ያሳዝናል፣ ላደረገልን ነግር ሁሉ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡

ዢሩ በክለብ ደረጃ በፈረንሳዩ ሞንፔሌ፣ በእንግሊዞቹ አርሰናል እና ቼልሲ እንዲሁም በጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ተጫውቶ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

በተጠናቀቀው የጣሊያን ሴሪ አ የውድድር ዘመን በኤሲ ሚላን የነበረውን ውል በማጠናቀቅ በነፃ ወደ አሜሪካ ክለቦች እንደሚያቀና በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡