ቴክ

በሞሮኮ በተካሄደ የሁዋዌ ቴክ ፎር ጉድ ክፍለ አህጉራዊ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ቡድን አሸነፈ

By Shambel Mihret

July 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞሮኮ በተካሄደው የሁዋዌ ‘ቴክ ፎር ጉድ’ ክፍለ አህጉራዊ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ቡድን አንደኛ በመሆን አሸንፏል።

ከምስራቅ፣ ሰሜን፣ ምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የተውጣጡ 17 ሀገራትን ያሳተፈ “የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር 2024” የቴክኖሎጂ ስልጠና መርሐ ግብር በሞሮኮ ኢሳውራ ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል።

ኢትዮጵያም ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 10 ተማሪዎችን በስልጠናው ያሳተፈች ሲሆን÷ አምስት ተማሪዎችን የያዘው የኢትዮጵያ አንድ ቡድን በሁዋዌ ቴክ ፎር ጉድ ክፍለ አህጉራዊ ውድድር ላይ አሸንፏል፡፡

ተሳታፊ ተማሪዎቹ በ28 ቡድኖች ተከፋፍለው ለውድድር የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ያዘጋጁ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ቡድን የሞሮኮ ቡድንን አስከትሎ አንደኛ ደረጃን በመያዝም አጠናቅቋል።

በዚህም ያሸነፉት ኢትዮጵያና ሞሮኮ በ2025 ለሚካሄድው ዓለም አቀፍ ፍፃሜ ወደ ቻይና ያቀናሉ ተብሏል።

ተማሪዎቹ በወቅቱ እንደገለጹት÷ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮረ ነው።

የሁዋዌ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሊሚንግ ዬ በበኩላቸው÷ የፕሮግራሙ ተልዕኮ ወጣቶች በፍጥነት የሚለዋወጥን ዓለም ለመጋፈጥ የሚያስችሉ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን እና አስተሳሰቦችን እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2008 በሁዋዌ የተጀመረው መርሐ ግብሩ ተሰጥኦን ለማዳበር፣ የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግና በዲጂታል ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ተሳትፎን ለማበረታታት እያገዘ መሆኑ ተገልጿል።

ሁዋዌ በኢትዮጵያ ፕሮግራሙን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚሰራም መገለጹን ከሁዋዌ ኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡