አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2016 የውድድር ዘመን ዋንጫ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በተዘጋጀ መርሐ ግብር ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ሌሎች የቡድኑ አበላት እንደ አፈፃፀማቸው ከ100 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሽልማት ከባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እጅ ተቀብለዋል።
አቶ አቤ ሳኖ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ ባንኩ በወንዶች እግር ኳስ ቡድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እጥፍ ድርብ ስኬቶች የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡
ሻምፒዮናው ቡድን በቀጣይ የውድድር ዓመትም ውጤቱን አስጠብቆ ለተሻለ እንዲተጋ በማሳሰብ የቡድኑ አባላት በሄዱበት የባንኩ አምባሳደር እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።
ባንኩ የስፖርት ማሕበሩን መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት አቶ አቤ ፥ በቀጣይም የጀመራቸውን የስታዲየም ግንባታ ሆነ ሌሎች ስራዎች ቅድሚያ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግርኳስ ቡድን አሰልጣኝ በፀሎት ልኡልሰገድ ፥ እንደ ቡድን የተገነባው ጠንካራ መንፈስ ለውጤት እንዳበቃቸው መግለጻቸውን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የቡድኑ አምበል ፈቱዲን ጀማል በበኩሉ የቡድኑ የጋራ ጥረት እና መናበብ ለሻምፒዮናነት እንዳበቃቸው ተናግሮ ፥ በቀጣይም የባንኩ አምባሳደር በመሆን ውጤታማነታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ተናግሯል።