የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በሱዳን ጉዳይ ከጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ

By Meseret Awoke

July 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከሱዳን ሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በሱዳን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ፥ ይህን አስመልክተውም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ በሱዳን የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት በሰላማዊ መንገድ መቋጨት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በወቅታዊ የሱዳን ጉዳይ ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከ744 ኪሎ ሚትር የሚዋሰኑ ጎረቤት ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የባህልና የምጣኔ ሃብት ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአንዱ ሀገር ችግር የሌላውንም የሚነካ በመሆኑ ለችግሮች የጋራ መፍትሄ በመሻት ለስኬቱም በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎችም ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለሀገራቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ የተለያዩ ጥረቶችን ስታድርግ መቆየቷን አስታውሰው ፥ በቀጣይም ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ በፊትም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ለሱዳን ህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሰላም እንዲያወርዱ ሲያግባቡ መቆየታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

በዛሬው ዕለትም በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከጄነራል አብደል ፈታህ አልቡርሃን ጋር የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሱዳን ወቅታዊ ችግር በውይይት እንዲፈታ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክርቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኘት ለሱዳን ህዝብ ያላቸውን ከበሬታ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።

ለሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እያደረጉት ላለው ጥረትም ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።