አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና መሃመድ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የለውጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳሰቡ፡፡
በዘላቂ ልማት ላይ በተካሄደው ከፍተኛ የፖለቲካ ፎረም ላይ ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና መሃመድ እንደተናገሩት፥ እንደ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና እጦት እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ “የለውጥ እርምጃዎች” አስፈላጊ እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኒውዮርክ በሚገኘው የተመድ ዋና ፅህፈት ቤት ለተገኙ ልዑካን እንዳስረዱት፥ ያሉት ተግዳሮቶች ከባድ ቢሆኑም በጋራ ማሸነፍ ይቻላል።
ሁሉም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ብቻ ሳይሆን የሚገባቸውን ሰላምና ብልጽግና ማሳካት እንችላለን ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ፖሊሲዎችን እና አዳዲስ መፍትሄዎችን ለመስጠትም ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።
ፎረሙ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለመዋጋት፣ ረሃብን ዜሮ ለማድረስ፣ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ሰላማዊ እና ሁሉን አቀፍ ማህበረሰብና የአተገባበር ዘዴዎችን በማጎልበት ላይ ትኩረት የተደረገባቸውን ጨምሮ በርካታ የዘላቂ ልማት ግቦች እድገትን ለመገምገም ያለመ ነው ተብሏል።
የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፓውላ ናርቫዝ፥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በተለይም ግጭት ባለባቸው ቀጣናዎች አስከፊ ፈተና መኖሩን ጠቁመዋል።