Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለማበረታታት በትኩረት መስራት ይገባል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለማበረታታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ በሁለተኛው “የሴቶች በዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ቀንን” አስመልክቶ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም÷ኢትዮጵያ የወጣት ሴቶችን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ለመጨመር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሜንተርሺፕ እየሰጠች መሆኑን አንስተዋል፡፡

እስካሁን ባለውም 1 ሺህ 500 ወጣት ሴት ተማሪዎች መርሐ ግብሩን መከታተላቸውን ገልጸው÷በሀገር ብሎም በአህጉር ደረጃ ወጣት ሴት ዲፕሎማቶችን ተሳትፎ ለመጨመርና ለማበረታታት በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ሴቶች በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ግጭት አፈታት ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በአምባሳደርነት፣ በውጭ ጉዳይና ሌሎች የዲፕሎማሲ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ÷ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ውሳኔ 1325 ትግበራ በብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር የሰጠችውን ትኩረትና ሒደት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

በውሳኔው የተቀመጡ ጉዳዮችን ከሀገሪቱ መርሐ ግብሮች ጋር በማጣጣም በሰላምና ጸጥታ፣ በሀገራዊ ምክክር፣ በአቅም ግንባታ፣ በውሳኔ ሰጪነትና ሌሎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ “የሴቶች በዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ ጥምረት” የተዘጋጀ ሲሆን አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version