Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በተለያዩ ከተሞች የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር በተለያዩ ከተሞች ተካሄደ።

የደስታ መግለጫ መርሃ ግብሩ በዛሬው እለት ከማለዳው ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ አዳማ፣ ቡራዩ፣ ሰበታ እና ቢሾፍቱ ከተሞች እንዲሁም በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ፣ በሀረሪ ክልል፣ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ፣ በሀዋሳ ከተማ እና በሌሎች ከተሞች ተካሂዷል።

በጅማ ከተማ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ላይ የጅማ ዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

በስነ ስርዐቱ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች፥ ሽልማቱ አንድነታቸውን እንደሚያጠናክርና በመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር እሴታቸውን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀመድና የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ፥ በሠላም ዘርፍ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ለመድገም የጅማ ከተማና የጅማ ዞን ነዋሪዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል የባህር ከተማ አስተዳደርም የዓለም የሠላም ኖቤል ተሸላሚ ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐብይ አህመድ የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በባህር ዳር እየተካሄደ ባለው የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ላይም የከልሉ አመራሮች፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ከባህር ዳር ከተማ የተወጣጡ የተለያዩ የህብርተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማም የደስታ መግለጫ መርሃ ግብሩ የሀረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች ወጣቶችና ሴቶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሰላም የኖቬል ተሸላሚ መሆናቸውን ተከትሎ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማም የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይም የወላይታ ዞን እና የሶዶ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሀብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩቤ፥ ሽልማቱ ሀገራችንን የመልካም ዝና ባለቤት ያደረገ ነው ብለው ለቀጣይ ትግል ስንቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ለሀገራችን የኩራት ምንጭ መሆኑን የጠቀሱት ሰልፈኞቹ በዚህም የወላይታ ህዝብ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ይህ እድልም ከአድዋ ድል ያልተናነሰና ሀገራቱን ወደ ከፍታ ማማ የሚያሸጋግር ተግባር ነው ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማም የደቡብ ክልል ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች እና አመራሮች ዛሬ የደስታ መግለጫ ፕሮግራም አካሄደዋል።

በደስታ መግለጫ ፕሮግራሙ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ከበደ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም የኖቤል ሽልማት ሰላማችንን ጠብቀን የተሻለች ሀገርን ለመፍጠር ቃል የምንገባበት ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የሰላም ኖቤል ሽልማት ላገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓት አካሄደዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ፥ “ በሰላም እና መረጋጋት ያገኘውን አንፀባራቂ ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ መስራት ይገባናል” ብለዋል።

የደስታ መግለጫ ዝግጅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማም ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት፥ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፉት 18 ወራት እንደሀገር የፈፀሟቸዉ ተደናቂ ተግባራት የሀገራችንን መፃኢ ዕድል በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችሉ ናቸው” ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የነበረውን አለመግባባት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት በመመለስ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ለማርገብና ቀጠናውን ከስጋት ነፃ ለማድረግ የፈፀሟቸው ተግባራት በእርግጥም ታላቁን የዓላም የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘት የሚገባቸዉ ታላቅ መሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

Exit mobile version