አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በአራት ክልሎች በተካሄደው የድጋሚና የቀሪ ምርጫ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብዛኞቹን መቀመጫዎች ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የድጋሚና የቀሪ ምርጫ ማካሄዱ ይታወሳል።
ቦርዱ ዛሬ የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ውጤት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል።
ይህን ተከትሎም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተካሄደው ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ብልፅግና 4፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 1 እንዲሁም የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 1 መቀመጫ አሸንፈዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ 60፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 3 እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 8 መቀመጫ አሸንፈዋል።
በአፋር ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ብልጽግና ፓርቲ 2 እና ለክልል ምክር ቤት 27 መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለክልል ምክር ቤት 3ቱንም መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉ ተገልጿል።
በሶማሌ ክልል በተካሄደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ 7 መቀመጫዎችን ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የድጋሚና የቀሪ ምርጫ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ቁሳቁስ ከማሟላት ጀምሮ በርካታ ሥራ ተሰርቷል።
መራጮች እውቀትን መሠረት በማድረግ እንዲመርጡ ግንዛቤ የማስጨበጥና ምርጫውን ለሚያስፈፅሙ አካላት ተገቢው ሥልጠና መሰጠቱንም ነው ያስረዱት።
ይህንንም ተከትሎ የድጋሚና የቀሪ ምርጫ በአራት ክልሎች፣ በ29 የምርጫ ክልሎችና በ1 ሺህ 218 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተካሄደ መጥቀሳቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የምርጫ ሂደቱም ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ እንደነበር ገልጸው ÷ የድጋሚና የቀሪ ምርጫ በተካሄደባቸው በአራቱም ክልሎች የመራጮች ተሳትፎ 85 በመቶ ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ÷ ቦርዱ የድጋሚና የቀሪ ምርጫን ለማካሄድ ጥናትን መሠረት ያደረገ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዚህም የምርጫ ክልል ጣቢያዎችንና ጽህፈት ቤቶችን በማቋቋም እንዲሁም በቂ ዝግጅት በማድረግ ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በታቀደው ጊዜ ማካሄድ እንደተቻለ ገልፀዋል።
በምርጫው 12 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 12 የግል ዕጩዎች መሳተፋቸውን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፥ምርጫውም ከፍተኛ የሆነ ፉክክር የተካሄደበት እንደነበር አስታውቀዋል።