ስፓርት

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሆነ

By Melaku Gedif

July 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሆነ፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ 30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የዋንጫውን አሸናፊ የለዩ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀን 9 ሰዓት ላይ ተካሂደዋል፡፡

በዚህ መሰረትም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የማሸነፊ ግቦች አዲስ ግደይና ሱሌይማን ሃሚድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሸነፍ አልያም ነጥብ መጣል እያሰበ ወደ ሜዳ የገባው መቻል ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ረትቷል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማሸነፉ መቻል የ80ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን በዋንጫ ለማጣጣም ሳይችል ቀርቷል፡፡