አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሸን ባንክ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ጋር በመተባበር በእንጦጦ ተራራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አከናውኗል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ችግኝ ተከላ ባንኩ በአካባበቢ ጥበቃ ዘርፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡
ዳሸን ባንክ ለተከታታይ ዓመታት በእንጦጦ ተራራ ላይ ሲያከናውን የቆየው ችግኝ ተከላ ሥራ ውጤት ማስመዝገቡንም አብራርተዋል፡፡
ባንኩ የእንጦጦ ተራራን ሥነ-ምህዳር ለማስቀጠል የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመው÷በዛሬው ዕለት በርካታ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ከዚህ ቀደም በእንጦጦ ተራራ ላይ የተከላቸው ችግኞች የጽድቀት መጠን ከፍተኛ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ ከዋናው መስሪያ ቤት፣ ቀጠና ጽ/ቤቶችና ቅርንጫፎች የተወጣጡ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች መሳተፋቸውን የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡